ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ለቡድን ሃያ አገራት በጻፉት ደብዳቤ ከኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የ150 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለአፍሪካ ጠይቀዋል።
ይህ ድጋፍ የአፍሪካን የድንገተኛ ጊዜ ጤና አገልግሎትን፣ ለበጀት ድጎማ፣ የውጪ ምንዛሬ ክምችትን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በወረርሽኙ ምክንያት የተጎዱ ንግድና ኩባንያዎችን ለመደገፍ ይውላል ብለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት ለወሰዱት ብድር የሚጠየቁት ወለድ እንዲሰረዝና ዝቅተኛ ገቢ ላለቸው አገራት እዳ በከፊል እንዲሰረዝም ጥያቄ ቀርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለቡድን ሃያ አገራት በጻፉት በዚህ ደብዳቤ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ለሚያካሂደው የማህበረሰብ ጤና አገልግሎትና የድንገተኛ ጊዜ ዝግጁነት ድጋፍ እንዲደርግለትም ይጠይቃል። የቡድን 20 አገራት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ በቀትታ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእዳ ቅነሳና ስረዛ በጠየቁበት በዚህ ደብዳቤያቸው ላይ አፍሪካ ወረርሽኙ ካደረሰባት ጫና ኩባንያዎቿንና ሠራተኞቿን ለመታደግ ያለባት እዳ ጫና ፈጥሮባታል ብለዋል።
” ኢትዮጵያ የአገራት ብድር ወለድ እንዲሰረዝ፣ በተጨማሪም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት እዳ እንዲሰረዝ ትጠይቃለች” ይላል ጠቅላእ ሚኒስትሩ ደብዳቤ።