በጀርመን መንግሥት የአፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ በተለይም ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ አሜሪካና አውሮጳውያን ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለማዳከም እና ለማፍረስ በርካታ ሴራዎችን ፈፅመዋል በማለት ወቅሰዋል::
124 ኛው የዓድዋ ድል በዓል እዚህ ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ዛሬ ተከብሮ ውሏል። በዓሉን በጀርመን የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ ነው ያዘጋጀው ። በበዓሉ ተጋባዥ ዕንግዳ የሆኑት በጀርመን መንግሥት የአፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ በተለይም ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ አሜሪካና አውሮጳውያን ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለማዳከም እና ለማፍረስ በርካታ ሴራዎችን ፈፅመዋል በማለት ወቅሰዋል::ዝርዝሩን እንዳልካቸው ፈቃደ አጠናቅሮታል::
ከሌሎች የአፍሪቃ አገራት ይልቅ የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና ከመቼውም ጊዜ በላይ አደጋ ላይ መውደቁን አንድ ኢትዮጵያዊ አንጋፋ የፖለቲካ ተንታኝ አስታወቁ:: በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ዛሬ በፍራንክፈርት ከተማ ባዘጋጀው 124ኛው የአድዋ የድል በዓል ዝግጅት ተጋባዥ ዕንግዳ የሆኑት በጀርመን መንግሥት የአፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ በተለይም ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ አሜሪካና አውሮጳውያን ኢትዮያን ከፋፍሎ ለማዳከም እና ለማፍረስ በርካታ ሴራዎችን ፈፅመዋል ሲሉም ወቅሰዋል:: የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቅኝ ግዛት ጭቆና ስር ለነበሩ አፍሪቃውያን እና የዓለም ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን የአድዋ በዓል ስናከብር በህዳሴው ግድብም ሆነ በአገሪቱ ህልውና ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን ሁሉ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ በጋራ በመመከት የአያቶቻችንን አኩሪ የታሪክ ገድል እንደግማለን ሲሉ ቃል ገብተዋል:: መንግሥት በአሁኑ ወቅት በህዳሴው ግድብ ድርድር ዙሪያ የወሰደውን አቋምም አድንቀዋል:: ከዚህ ሌላ መጪው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚካሄድ ከሆነ መንግሥት ወደ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሥርዓት አሻግራችኋለሁ በማለት የገባውን ቃል በማክበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በነፃነት የሚሳተፉበትን ምርጫ እንዲያካሂድም ጠይቀዋል:: ዝርዝሩን እንዳልካቸው ፈቃደ አጠናቅሮታል::
እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 1884-85 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት እዚህ ጀርመን በርሊን ከተማ በመጀመሪያው የአገሪቱ መራሄ መንግስት ኦቶ ፎን ቢስማርክ አስተባባሪነት 13 የአውሮጳ ኃያላን አገራትና ዩናይትድስቴትስ አፍሪቃን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት የቃል ኪዳን ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ የኢጣሊያ መንግሥት የጦር ኃይሉን ዘመናዊ መሳሪያ አስታጥቆ ኢትዮጵያን እንደወረረ በጀግኖች አርበኞች ቆራጥ ገድል ድል የተመታበት 124ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በፍራንክፈርት ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል:: ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ልዩልዩ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በማድረግ እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን አያሌ የተግባር እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውን የቆየው የዕለቱ ዝግጅት አስተባባሪ በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ሊቀመንበር አቶ አፈወርቅ ተፈራና ሌሎቹም የማህበሩ አመራሮች “ኢትዮጵያውያን ዘር እና ሃይማኖት ሳይለያቸው ዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰው በወራሪው ጦር ላይ ድልን በመቀዳጀት በአፍሪቃ ብቸኛዋ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ታሪካዊት አገር እንዳወረሱን አስታውሰው ፤ ዛሬም የኢትዮጵያን አንድነትና የሕዝቦቿን ሰላም የማይፈልጉ ኃይላት የህዳሴውን ግድብ አስታከው የከፈቱብንን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንደቀድሞው ሁሉ የፖለቲካ የብሄርና የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን በጋራ በመመከት ዳግም ታሪክ በመስራት የአገራችንን ህልውና ልናስጠብቅ ይገባል ፤ በግድቡ ግንባታም ሆነ የውሃው ሙሌት ላይም ቢሆን ህጋዊ መብታችንን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::
የዕለቱ የክብር እንግዳ በጀርመን መንግስት የአፍሪቃና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የፖለቲካ አማካሪና ተንታኝ የሆኑት ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተካሳ በተለይ ከዶይቼ ቨለ “DW” ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ,ኢትዮጵያ አሁን ላይ ውዝግብ ውስጥ የገባችበት የህዳሴው ግድብ ከጂኦ ፖለቲካ ስትራቴጂ ጠቀሜታ አኳያ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ መገንባቱ በሂደት የሚያመጣው ውዝግብ ግምት ውስጥ አለመግባቱ ,የደለል ክምችትንና አደጋን ከመቀነስ አኳያም በአሁኑ ወቅት ዓለማቀፍ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው የትናንሽ ግድቦች ግንባታ አማራጭ ተግባራዊ አለመሆኑ እና በሌሎችም የቴክኒክ ጉድለቶች ምክንያት የተለየ አመለካከት እንዳላቸው ገልፀው ከዚህ ይልቅ በተለይም ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ አሜሪካና አውሮጳውያን ፈፅመውታል ያሉት የተቀነባበረ ኢትዮጵያን የማፍረስና ህልውናዋንም አደጋ ላይ የመጣል ሴራ ከየትኛውም የአፍሪቃ አገራት ይልቅ ዛሬ ልትወጣው ከማትችልበት አሳሳቢ አደጋ ውስጥ ከቷታል በማለት መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ አፅንዖት ሰጥቶ ይህንኑ ጊዜ የማይሰጥ ችግር ለመፍታት አገር የማዳኑን ተግባር ቅድሚያ ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል::
ያነጋገርናቸው የዝግጅቱ ታዳሚዎችም መላው አፍሪቃውያን የካሪቢያን አገራትና በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሕዝቦች ሁሉ ዳር እስከዳር በወራሪ ቅኝ ገዢዎች ላይ የነጻነት ትግል እንዲያቀጣጥሉ ፈር ቀዳጅ የሆነው የጀግኖች አያቶቻችንን ታሪካዊ የአድዋ ገድል ከመዘከር ጎን ለጎን እኛም ልጆቻቸው ዛሬም እጅ ለእጅ ተያይዘን ሌላ አንፀባራቂ ታሪክ የምንሰራበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል:: “ኢትዮጵያውያን ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ወደጎን ትተን አገርን በመውደድና ዳር ድንበር በጠላት እንዳይወረር በማስከበር የቀደሙት አያቶቻችንን የታሪክ ገድል በመድገም የመንፈስ ልጆቻቸው መሆናችንን ማስመስከር ይኖርብናል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል:: ከዚህ ሌላ ታዳሚዎቹ መንግስት በደምቢደሎ ለታገቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል::
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ ባዘጋጀው 124ኛው የአድዋ ድል በዓል ፤ የጀግኖች አርበኞችን ገድል እና የአገር ፍቅርን የሚያወሱ ወኔ ቀስቃሽ ግጥሞች አንድነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ መልዕክቶች በሀገሬ የባህል ቡድን የተዘጋጁ ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎች እንዲሁም በጀርመን ኑሮዋን የመሰረተችው አንጋፋዋ አርቲስት አልማዝ ልመንህና ሌሎችም የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች የአድዋን ድል የሚዘክር አጭር የመድረክ ተውኔት ለታዳሚው አቅርበዋል:: በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የለውጡን ስኬት እና ተግዳሮቶቹን በተመለከተ እንዲሁም ስለመጪው አገራዊ ምርጫ ተስፋና ስጋቶች ተሳታፊዎች ላነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ ማብራሪያ ሰተዋል:: ከዚህ ሌላ የማህበሩ አመራሮች መጪው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚካሄድ ከሆነ መንግሥት ወደ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሥርዓት አሻግራችኋለሁ በማለት የገባውን ቃል በማክበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በነፃነት የሚሳተፉበትን ምርጫ እንዲያካሂድም ጠይቀዋል:: በዝግጅቱ ላይ በጀርመን የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቶችም ተካፋይ ሆነዋል:: የኢጣሊያ ወራሪ ሰራዊት በአድዋና በማይጨው ጦርነቶች በፈፀመው ጥቃት ከ 1 ሚልዮን በላይ ዜጎቻችን በመርዝ ጭስ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ እና በአውሮፕላን የቦምብ ድብደባ ማለቃቸውን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ::
እንዳልካቸው ፈቃደ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ