የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመርያዎቹ 100 ቀናት

ፖለቲካ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመርያዎቹ 100 ቀናት
11 July 2018
ብሩክ አብዱ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ መሳብ ችለዋል፡፡ አገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት በተለይ አንድነት፣ ፍቅርና ይቅርታ ላይ አተኩረው ሲሠሩ 100 ቀናት ሞልተዋቸዋል፡፡

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በመተካት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. አንድ መቶ ቀናቸውን ይደፍናሉ፡፡ እነዚህ አንድ መቶ ቀናት በተለይ በአሜሪካ ከ32ኛው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ጊዜ ጀምሮ፣ የአንድን ፕሬዚዳንት የሥራ እንቅስቃሴዎች ለመለካትና ቃል የተገባባቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም ምን ያህል ርቀት ይጓዛል የሚለውን ለመገምገም በመለኪያነት የሚውሉ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመጀመርያ ንግግራቸውና ከዚያ ቀደም ብሎ በሚኖራቸው የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት የሚያደርጓቸውን ነገሮች በዝርዝር አቅርበው የሚለኩባቸው ሲሆን፣ የመጀመርያዎቹ አንድ መቶ ቀናት ከፍተኛ ትኩረት የሚደረግባቸውና ፕሬዚዳንቱም በጥንቃቄና በፍጥነት የሚንቀሳቀስባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያና የአሜሪካ የፖለቲካ አደረጃጀትና ቅርፅ የተለያየ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ያከናወኗቸውን ተግባራት ለሚታዘቡ ድርጊቶች የሄዱባቸው ፍጥነትና የድርጊቶቹ ብዛት ብሎም ያገኙት ትኩረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የ100 ቀናት የሥራ እንቅስቃሴ በግልጽ ለማየት ያስችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ለአንድ ሳምንት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በፈቃዳቸው ከግንባሩ ሊቀመንበርነትና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የለቀቁትን አቶ ኃይለ ማርያምን በመተካት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሊቀመንበር መሆናቸው ይፋ አደረገ፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ የሚመረጥ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ እንደሚሰየም የፓርቲው አሠራር ስለሚፈቅድ፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ፓርላማው ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ሥልጣቸውን ከለቀቁት አቶ ኃይለ ማርያም ጋር የሕገ መንግሥትና የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተተኩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸው በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሰፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ይህ ንግግራቸውም በቀጣይ ለሚሠሯቸው ሥራዎች አቅጣጫዎችን ያመላከቱበት ነበር፡፡ የመላውን ሕዝብ ትኩረትና ቀልብም ስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ‹‹ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት ዓበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው። ክስተቱ በአንድ በኩል በአገራችን ዘላቂ፣ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የሕገ መንግሥትታዊ ሥርዓት መሠረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በሕዝብ ፍላጎት ሕዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑ ያመለክታል፤›› በማለት፣ እያንዳንዱን የአገሪቱ ችግር እንዴት ለመፍታት እንደሚቻል አመላክተው የሌሎች ድርሻም ምን መሆን እንዳለበት አስምረውበታል፡፡

ከንግግራቸው በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት በርካታ ጉብኝቶችንና ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ነዋሪዎች ጋር በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር ውስጥ ጉዞዎችና ውይይቶች

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቃለ መሃላ በፈጸሙ በአምስተኛ ቀናቸው የመጀመርያው የአገር ውስጥ ጉብኝታቸው መዳረሻ አድርገውት የነበረው የሶማሌ ክልልን ነው፡፡ በክልሉ መዲና ጅግጅጋ በነበራቸው ቆይታ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭት ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉብኝታቸው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን ይዘው የተጓዙ ሲሆን፣ የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በአዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ እንዲሠሩ፣ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች ትራክተር በመዋዋስ እንጂ በሌላ ጉዳይ መጋጨት እደማይገባቸው አሳስበዋል፡፡

ከሶማሌ ክልል ጉዟቸው በመቀጠል ሁለተኛ የአገር ውስጥ ጉብኝት መዳረሻቸው ያደረጉት ባለፉት ሦስት ዓመታት በብጥብጥ ስትታመስ የነበረችው አምቦ ከተማን ነው፡፡ በአምቦ በነበራቸው ቆይታ በርካታ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችን ይዘው በመገኘት፣ ‹‹አንድነታችንን አጠናክረን የአገራችንን ዕድገት ማፋጠን አለብን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አቶ ዓለማየሁ እሬንሶ የተባሉ የአምቦ ነዋሪ፣ ‹‹አሁን ያየሁት ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ማሳያ ነው፡፡ ይህች አገር የሁላችንም የጋራ አገር ናት፤›› ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀጠል በትግራይ ክልል መቀሌ፣ እንዲሁም አማራ ክልል ጎንደርና ባህር ዳር ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ አንድነትን እንገንባ፣ መከፋፈልን እናስቀር የሚሉ መልዕክቶችን ያዘሉ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከብሔር ተኮርነት ይልቅ ለአገር ትኩረት አድርገን እንሥራ በማለት ጥሪያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በመቀሌ በነበራቸው ቆይታም አካባቢያዊ ጉዳዮችን፣ በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበረውን ሰላማዊ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚሠሩ አስታውቀው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ ጉብኝት በማድረግ፣ በሐዋሳም በነበራቸው ቆይታ ተመሳሳይ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተጓዙ ሲያደርጓቸው ከነበሩ ውይይቶችና ንግግሮች በተጨማሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአዲስ አበባ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶችን አድርገው ነበር፡፡

የመጀመርያው በሚሊኒየም አዳራሽ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት ንግግር ሲሆን፣ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን የይቅርታና የዕርቅ ተግባራት እንደሚያከናውኑም ገልጸው ነበር፡፡ ሰፋፊ አገራዊ ጉዳዮችንም መዘርዘራቸው ይታወሳል፡፡ የአገሪቱ ሀብት ሕዝቦቿ እንደሆኑ ጠቁመው፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመተማመን ተፈጥሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይገታ፣ ሁሉም በአገራዊ ኃላፊነት ለአገሩ ዘብ እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከሚሊኒየም አዳራሽ ውይይት ማግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር ውይይት ሲያደርጉ የንግድ ማኅበረሰቡ ሥራውን በሀቀኝነት እንዲሠራ፣ ከአገር በማሸሽ በዱባይና በቻይና ያስቀመጡትን ዶላር እንዲያመጡ ባለሀብቶችን አሳስበው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ውይይታቸው ወቅት የንግዱ ማኅበረሰብ አሉብኝ የሚላቸውን ችግሮች ያነሳላቸው ሲሆን፣ እሳቸውም በመድረኩ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች በዝርዝር እንዲቀርቡላቸው አሳውቀው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ማይንድ ሴት በተባለ ድርጅት የተዘጋጀ የታላላቅ ሐሳቦች ኮንቬንሽን ላይ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጉብኝታቸው መልስ በድንገት በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በአሮጌ አስተሳሰብ አዲሱን ትውልድ መምራት እንደማይቻል፣ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በጋራ ለማልማት እንሥራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ አገር ጉዞዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የመጀመርያ የውጭ አገር ጉዟቸው መዳረሻ የነበረችው ጂቡቲ ስትሆን፣ በጂቡቲ በነበራቸው ቆይታ ወደብንና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን መሠረት ያደረጉ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም ጉዟቸው ኢትዮጵያ በጂቡቲ የወደብ ልማት እንድትሳተፍ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ አትራፊ በሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የጂቡቲ መንግሥት ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ ስምምነት ተደርጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለው ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሱዳን ጉብኝት ሲያደርጉ፣ በሱዳንም በጂቡቲ የተደረገውን ዓይነት የወደብ ስምምነት አድርገው፣ ከአራት ቀናት በኋላ ወደ ኬንያ በማቅናት እንዲሁ ኢትዮጵያ በኬንያ ወደብ ለማልማት የሚያስችላትን ስምምነት አድርገው ተመልሰዋል፡፡

ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብፅ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከግብፅ መንግሥት ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ግብፅን በምንም ዓይነት ሁኔታ ለመጉዳት እንደማትፈልግ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አንድ ስኬት የታየላቸው፣ ለጉብኝት በሄዱባቸው አገሮች ሁሉ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ማስፈታታቸው ነው፡፡ ከግብፅ ያስፈቷቸውን እስረኞች እሳቸው በሚጓዙበት አውሮፕላን ጭነው ማምጣታቸው በርካቶችን አስደንቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ካደረረጓቸው ጉብኝቶች ውጪ በሳዑዲ ዓረቢያና በተባሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጉዞዎችን በማድረግ በእነዚህ አገሮችም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ በነበራቸው ቆይታ አሥር ጥያቄዎችን ይዘው በመገኘት ከእዚህ ውስጥ ዘጠኙ መልስ ያገኙ ሲሆን፣ አንዱ ማለትም ሼክ መሐመድ አል አሙዲንን ለማስፈታት የጠየቁት ጥያቄ ብቻ መልስ ሳያገኝ መመለሳቸውን፣ ነገር ግን በዚህም ጉዳይ ላይ ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ከሁለቱም አገሮች ለኢትዮጵያ ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪና የነዳጅ ድጎማ ማግኘታቸውም መሰማቱ ይታወሳል፡፡

ፖለቲካ

ጠቅላይ ሚነስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ትኩረት አድርገው ከሠሯቸው ጉዳዮች መካከል የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም ካቢኔያቸውን ከማዋቀር አንስቶ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና በውጭ አገር የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው፣ ይኼንንም ጥሪ በመቀበል ወደ አገር ውስጥ የገቡትን ተቀብለው ማነጋገር ያካተቱ ነበሩ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የተዋቀረ ሲሆን፣ ብዛት ያላቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ያሉ ሚኒስትሮችን፣ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችንና ዳይሬክተሮችን በአዳዲስ ተሿሚዎች ተክተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ16 ሚኒስትሮችን ሹመት በፓርላማው ያፀደቁ ሲሆን፣ ለሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች ሹመቶችንም ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩትን ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በጡረታ እንዲሸኙ አድርገው፣ በእሳቸው ቦታ ጄኔራል ሰዓረ መኰንንን የሾሙ ሲሆን፣ ለረዥም ዓመታት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርነት ሲሠሩ የቆዩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን በጄኔራል አደም መሐመድ ተክተዋቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉት ጥሪ የብዙዎቹን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው የፓርላማ ንግግር ወቅት፣ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ የሐሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሐሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመሥርተን መግባባት ስንችል የሐሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሐሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሔ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም … አገር ይገነባል። የእኔ ሐሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳል። ያለችን ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ አገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረ ብሔራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ቀጥለውም በውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚ ሳይሆኑ ተፎካካሪ ስለሆኑ፣ ወደ አገራቸው ገብተው እንዲፎካከሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሠረት፣ ‹‹ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ እንደ መጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግሥት በኩል ፅኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ፣ ስለሰላምና ፍትሕ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና አገራዊ ፍቅር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ይኼንን ጥሪ ተከትሎ መጀመርያ ከኦነግ በመገንጠል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) በሚል ስያሜ ፓርቲ አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሊቀመንበሩ አቶ ሌንጮ ለታ፣ ምክትል ሊቀ መንበሩ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) እና ሌሎች ልዑካንን ያቀፈ ቡድን ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሌሎች የፓርቲና የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ከኦዴግ በኋላም የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡

ይበልጥ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያሰፋሉ በሚል እሳቤም፣ በእስር ላይ የነበሩትን የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር የነበሩትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች 575 እስረኞች እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡

ኢኮኖሚ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኢኮኖሚው በልማታዊ መንግሥት መርሆዎች ተመሥርቶ ያስመዘገባቸው ውጤቶችን ዕውቅና ሰጥተው፣ አገሪቱ ካጋጠሟት የውጭ ምንዛሪና ሌሎች ችግሮች ለማውጣት የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግምገማ በማድረግ ዕርምጃ እንደሚወስዱ፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን በማጠናከርና ግብርናውን በማዘመን ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የፖሊሲ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረው ነበር፡፡

ምንም እንኳን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጋማሽ ግምገማ የተካሄደና የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት አስቸጋሪ እንደሆነ ቢገለጽም፣ አገሪቱን ካጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማስወጣት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር በተረደገ ስምምነት፣ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታና የሁለት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማግኘት መቻላቸው ተገልጿል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረትና መዋቅራዊ ማነቆ ለመፍታትም የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ኢትዮ ቴሌኮምን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የምድር ባቡር ኮርሬሽንና ሌሎች መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማስተላለፍ የወሰነ ሲሆን፣ ይኼንንም ለማድረግ ጅምር እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡

ሠልፍ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ አጭር ጊዜያት ያመጧቸውን ለውጦች በመደገፍ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የምሥጋና ሠልፍ የተደረገ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሠልፉ ላይ በመገኘት በተለይ በክልላዊ ወሰኖች ምክንያት የሚያጋጥሙ ግጭቶችን በማውገዝ፣ ፍቅር እንዲሰፋና ኢትዮጵያዊነት እንዲነግሥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በሠልፉ ማብቂያ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 154 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ ሠልፎች ሲደረጉ ሰንብተዋል፡፡

ዲፕሎማሲ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች መካከል ትኩረት ሊስብ የቻለው አንዱ ድርጊት የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ያለንበት ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ በቀውስ ውስጥ ያለበት፣ ብዙ የየራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ ያላቸው ኃይሎች የሚራኮቱበት፣ ውስብስብ መጠላለፍ በቀጣናው ያለበት ወቅት ነው። በዚያው ልክ ደግሞ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረዥም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ያለንበት አካባቢ ነው፡፡ የውጭ ግንኙነታችንን በተመለከተ አገራችን የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት፣ የአፍሪካ ኅብረት መሥራችና መቀመጫ፣ የቀድምት ዓለም አቀፍ ተቋማት መሥራችና በዓለም አቀፍ፣ በአኅጉር አቀፍ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህና ገንቢ ሚና የምትጫወት አገር ናት። ይኼንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሠረተውን ፖሊሲያችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። ከአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ወንድሞቻችን ጋር በአጠቃላይና ከጎረቤቶቻችን ጋር በተለይ በችግርም በተድላም አብረን እንቆማለን። ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለት አገሮች ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስዱ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ የአልጄርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለውና የድንበር ኮሚሽንንም ውሳኔ ለመተግበር ዝግጁ እንደሆነ ወስኗል፡፡

ይኼንንም ውሳኔ ተከትሎ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ የማነ ገብረ መስቀል አዲስ አበባ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ከኤርትራ ልዑካን ጋር የነበረውን ውይይት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሰላምና የደኅንነት፣ ብሎም በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ጦርነት በይፋ ማብቃቱን በስምምነት አትመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባደረጉት ስምምነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረራ እንደሚጀምር፣ ሰዎች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው መሄድ እንዲችሉ፣ ብሎም ወደቦች ለሁለቱም አገሮች አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ተደርሷል፡፡ ሌሎች ስምምነቶችም ተደርገዋል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ መገናኛዎች ሳይቀር ከፍተኛ ሽፋን ያገኘ ጉብኝት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንዳስገኘላቸው በስፋት እየተነገረ ነው፡፡

ፈተናዎች

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ታይቶ የነበረው ሰፋ ያለ ግጭት የረገበ ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት የክልልና የዞን ወሰኖችና ሌሎች ምክንያቶች በየቦታው እየፈነዱ አዳዲስ ግጭቶች ይታያሉ፡፡

በምዕራብ ጉጂና በጌዴኦ፣ በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በወልቂጤ፣ በቤንች ማጂና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳና ሌሎች ከተሞች የተከሰቱ ግጭቶች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳቶችን አስከትለዋል፡፡

እነዚህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶች የመጀመርያዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተናዎች ሲሆኑ፣ ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው ሥፍራዎች ከኅብረተሰብ ጋር ተወያይተው የዞኖችና የወረዳዎች አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲለቁም አሳስበዋል፡፡ በማሳሰቢያው መሠረት ከኃላፊነታቸው የለቀቁ አሉ፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው ሲሆኑ፣ ከሁሉም በላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ አመኔታና ፍቅር አግኝተዋል፡፡ ሕዝቡም በሰላማዊ ሠልፎችም ሆነ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ በመስጠት ላይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአስመራ የኤርትራ ሕዝብ ያደረገላቸው አቀባበልና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሁኔታ ይኼንን አባባል ያረጋገጠ ይመስላል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምልከታም ተሰሚነታቸውንና የዲፕሎማሲ ስኬታቸውን ያሳያል እየተባለ ነው፡፡

Recommended For You

About the Author: admin