ከኢትዮ-ጀርመን ግብረ ኃይል ለፍትሕና ለእኩልነት ማኅበር የተሰጠ አስቸኳይ ማሳሰቢያ!!!
ለሚመለከታቸው በሙሉ፤
የአማራን ማኅበረሰብ ተፈጥሮአዊ ማንነትን በማንቋሸሽ፣ በማጥላላት፣ ጥላቻን በመዝራት አመጽን በማኅበረሰብ ላይ የሚቀሰቅሱ የጥላቻ ሙዚቃዎችን ፣ ንግግሮችንና መፈክሮችን ይመለከታል። እንደሚታወቀው ወያኔ ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በሚገዛበት ጊዜና ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በብልጽግና ኦነግ አገዛዝ የኦሮሙማን ርዕዮተ- ዓለም እንደ ዋና መመሪያው ያደረገው የብልጽግና አገዛዝ የሀስት ትርክትን እንደ ዋና ምክንያት በመጠቀም በተፈጠረው የጥላቻ መስፋፋት ምክንያት የማኅበረሰቡ አካል የሆኑ ንጹኃን ዜጎችን በተለይም ከአማራው ማኅበረሰብ የሚወለዱ ለብዙ ዓመታትና ከትውልድ ወደ ትውልድ በተላለፈ፣ በሰላምና በፍቅር ከኖሩበት ቀያቸው በተቀነባበረ መልክ መንግሥታዊ መዋቅር በመጠቀም የአማራውን ነገድ ሃይማኖት ሳይለይ ሲፈናቀሉ ሀብት ንብረታቸው ተነጥቆ የቀረው ተዘርፎ ሕጻናት ያለ አሳዳጊ አቅመ ደካማ አረጋውያን ደግሞ ያለ ጧሪና ቀባሪ ሲቀሩ ለከፋ ጉዳትና እንግልት ሲዳረጉ አይተናል:: ብዙዎችም ለከፋ ስደትና በየመጠለያ ድንኳን በረሀብና በበሽታ አልቀዋል። አሁንም ይህ አሳዛኝ ድርጊት ቀጠለ እንጂ አልተቋረጠም። ይባስ ብሎ ትጥቅ በማስፈታት ስም የወረራ ጦርነት ተከፍቶ ከላይ በድሮን ከታች በምድር ደግሞ በከባድ ተምዘግዛጊና ተወጫፊ መሣሪያ በመተኮስ ንጽኃን እየተጨፈጨፉ ከተማ እየወደመ ዜጎች ቤት አልባ መሆናቸዉን የ ዓለም ሕዝብ አይቶታል። ይህም የተደረገው የዜጎችን ሕልውና ለመጠበቅ ተመርጫለሁ በሚለው አገዛዝና የሲቪል ማህበራት ባሉበት አገር በመሆኑ ድርጊቱን እጅግ አሳዛኝ ያደርገዋል። ማንኛውም ጤነኛ ሰው በንጹኃን ላይ የሚደረግን ግፍና በደል እያየ ማለፍ አልነበረበትም። አሁን ማኅበራችን ይህንን ማሳሰቢያ ለመጻፍ ያነሳሳው በቅርቡ ለሕዝቡ መንግሥት በሚጠቀምበት ሚድያ በሕዝብ ግብር ክፍያ በሚተዳደር መገናኛ ብዙኃን በተለቀቀው ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ጠብን የሚዘሩ አንድን ማኅበረሰብ ነጥሎ በመስደብ የተዘፈኑ የኦሮሞኛ ሙዚቃዎች በአስቸኳይ መቆም አለባቸው:: ዘፋኞቹም ለሕግ መቅረብ አለባቸው:: ይህ ዓይነቱ አንድን ማኅበረሰብ የሚጎዳና መጨረሻም ወደ እርስ በርስ መተላለቅ የሚያመራ ቅስቀሳና ነውረኛ ተግባር እዚህ ባለንበት ሀገርና ክፍለዓለም በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው ። ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የፈለገዉን ልብስ በፈለገው ቀለም የመልበስ ወይም የመያዝ ሰብአዊ መብቱ ስለሆነ በኦሮሙማ መንግስት ፖሊሶች ለምን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ለበሳችሁ እየተባለ የሚደረገው ወከባ አሁኑኑ መቆም አለበት:: የመንግሥት ኃይልም የእያንዳንዱን ዜጋ ክብር የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። በአጠቃላይ በተባበሩት መንግሥታት በተደነገገው የሰብአዊ መብት ድንጋጌ መሠረት የሰውን ልጅ ከሕግ አግባብ ውጭ መብቱ መነካት የለበትም። ይህም ማለት ማንኛውም ማኅበረሰብም ሆነ ግለሰብ በሰላማዊና በፍትሐዊነት የመኖር መብት አለው። በአንድ አገር ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመዘዋወርና ራሱን የማሳደግ መብቱ የተጠበቀ ነው። ስለሆነም ማንኛውም የሲቪል ማኅብረሰብ ሆነ የመንግሥት አካል እንደዚህ ዓይነቱ መንፈስን የሚረብሽ፣ ሰላምን የሚነሳና፣ አንድን ማኅበረሰብ በሌላኛው ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ማንኛውንም የጥላቻ ቅስቀሳ የሚያደርግ በፍጥነት እንዲቆም ማድረግና ፈጻሚውን ግለሰብም ሆነ ቡድን በሕግ ፊት ተጠያቂ መደረግ አለበት። ለወደፊቱም ይህንን ዓይነቱን የጥላቻ ቅስቀሳ የማያደርግ፣ ቀስቃሹንም ለፍርድ የማያቀርብ የመንግሥት አካል ሆነ ይህንን ተቀብለው በብዙኃን ሚዲያ የሚያስተላልፉ የወንጀሉ ተባባሪ እንደሆኑ በግልጽ የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝተነዋል ። ስለዚህ ማንኛውም በዜግነት ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ ከፍትሕና ከእውነት ጋር እንድንቆም ጥላቻን የሚሰብኩ ጠብን የሚዘሩ እኩያንን ግለሰቦችን ለመቃወም በአንድነት እንድታገላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን። ፍትሕ ለተገፋው የአማራ ሕዝብ !