ጀርመን እንዴት ኮሮና በሽታን እንደተቋቋመች !

ጀርመን በአሁኑ ሰዓት የተመዘገቡ ከ160ሺ በላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሲገኙ፣ ከ6ሺ በላይ ህይወታቸው አልፏል። ከ120ሺ በላይ ሲያገግሙ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ምርመራዎች ተደርገዋል። ቢሆንም እስካሁን እንደተፈራው ወረርሽኙ ሃኪም ቤቶችን አላጨናነቀም። 20ሺ ከሚሆኑ የፅኑ ህሙማን አልጋዎች መካከል 13ሺ የሚሆኑት እስካሁን ጥቅም ላይ አልዋሉም። ይህም ሆኖ ጀርመን ይህንን ወደ 40ሺ ከፍ ለማድርግ እየሰሩ ሲሆን በበርሊን የኢክስፖ ቦታ ላይም የኮሮና ሆስፒታል ተገንብቶ ዛሬ ተጠናቋል። ጀርመን ውስጥ በብዙ ሺ ከሚቆጠሩት ክሊኒኮች በተጨማሪ ወደ 2ሺ የሚጠጉ ትልልቅ ሆስፒታሎች ይገኛሉ። እነዚህም ስራቸውን ለሌላ ፅኑ ህሙማኖች መልሰው ክፍት አድርጋዋል። በአሁን ሰዓት አንድ ሰው የሚያሲዘው 0.76 ደርሷል። ወይም 4 የተያዙ ሰዎች 3 ሰዎችን ያስይዛሉ ማለት ነው። ጀርመን 4.5 ሚሊዮን ምርመራዎችን በየሳምንቱ ለማድረግ እቀድ ሲኖር፣ ለዚህም ወደ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ በወር ለመመደብ ታቅዷል። ፈረንሳይን ከወሰድን የወረርሽኙን ምርመራ ወደ 700ሺ በሳምንት ለማሳደግ አቅዷል። የጀርመኑ ሮበርት ኮህ ኢንስቲትዩት ሰዎች ምርመራ ተድርግው ኔገቲቭ መሆናቸው ካርጋግጡ በኋላም ወደቤታቸው ሲመልሱ ወይም በሌላ አጋጣሚ ሊይዛቸው የማይችልበት ምክንያት ስለሌለ ደጋግሞ መመርመርን መክሯል።

 ጀርመን 10 ሚሊዮን ሰዎች አጭር ሰዓት ስራ „Kurzarbeit“ ገብተዋል። አጭር ስራ ማለት ከተቀንሰ የስራ ሰዓት እስከ ምንም አለመስራትን ያጠቃልላል። ከ725 ሺ በላይ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን 60 ፕርሰንት ደሞዛቸውን በሚያገኙበት መልኩ ቤታቸው እንዲቀመጡ እና የመንግስትን እርዳታ ለማግኘት ማመልከታቸው አይረሳም። ይህ ከቤት-ቤሮ Home office ስራ ጋር አይገናኝም። ወደ 70ሺ የሚሆኑ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ባሮች ምናልባትም መልሰው ሊያገግሙ በማይችሉበት ሁኔት ሊከስሙ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ።

 ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ ጀርመን ታይቶ ለማይታውቅ የኢኮኖሚ ቀውስ (Rezession) ተጋርጧል። በ1930ዎች የነበርው ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ (Great Depression) ተመሳሳይነት በተለያዩ አገራት ላይ ሊከሰት እንደሚችል እየተጠቀስ ሲሆን ለምሳሌ ከ27 አገራት የተወጣጣው የአውሮፓ ህብረት GDP በያዝነው 2020 በጥር እና በመጋቢት መካከል በአስደንጋጭ መልኩ በ3.5 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህ ደግሞ በፈረንሳይ፣ በጣልያን እና በስፔን ላይ በከፈተኛ ደርጃ የወርደ ነው።

 የጀርመን የኢኮኖሚ ሳይኮሎጂስቶች እንደሚመክሩት በየሚዲያው ላይ የሚነገርው ለወደፊት ስለሚመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ ዜና በእራሱ ችግር የሚፈጥር እና ቀውሱን የሚያፋጥን መሆኑን ነው። ኢኮኖሚ እና ሳይኮሎጂ ተቆራኝተው የሚሄዱ፣ ሳይኮሎጂ በኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴዎች፣ ባህሪዎች ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ይዘት ያለው ሲሆን፣ ከወረርሽኙ በኋላ ሊመጡ ስለሚችሉ መልካም ነገሮች፣ ለኢንቨስትመንት የሚያነሳሱ የሚዴያ ሪፖርቶች ቢቀርቡ ይመከራሉ። ቀውሶች የተፋጠነ የለውጥ ደረጃዎች ናቸው ብለው የሚያምኑ የኢኮኖሚ ጠበብቶች ብዙ አዳዲስ ነገሮች በችግሮች ውስጥ ይወጣሉ፣ ያረጁ ነገሮች ይጠፋሉ፣ ቀውስ ሲያልፍ አዲስ አጋጣሚም ሊምጣ እንደሚችል ይገልፃሉ። የፖለቲካ ሳይኮሎጂስቶች በበኩላቸው የጀርመን ፖለቲከኞችን ባህሪይ በወረርሽኙ ቀውሱ ያሳዩትን ተሳትፎ በማጥናት ፕሮፊሽናል ፖለቲከኞች ከፍተኛ መረጋጋት፣ ማርጋጋት፣ አእምሮዊ ብርታት፣ ዲስፕሊን እና የማስፋፀም ብቃት እንዳላቸው አስመስክረዋል ብለዋል።

 ጀርመን ከላይ እንደተጠቀስው ታይቶ ወደማይታወቅ የኦኮኖሚ ቀውስ እየገሰገስች ቢሆንም የጀርመን መንግስት (የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር) በቅርቡ ለኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት በኢኮኖሚው ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ማስተካከያ ወደ 120 ሚሊዮን ዩሮ ያህል እንደሚረዳ የገለፀ ሲሆን በጀርመን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም የተለያየ እርዳታ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ። ይህም አንድነት፣ አብሮነት እና መርዳዳት ምን ያሀል አስፈላጊ መሆኑን ሲያሳይ የአንድ አገር አኮኖሚን የሚያጠናክረው በብቸኝነት መበልፀግ ሳይሆን ከሌሎች ጋር ሲተባበር መሆኑን ያሳያል።
……….
ቻንስለር ሜርክል በዛሬው እለት ቀጣዩን በጥንቃቄ የማላላት እርምጃዎችን ገልፀዋል። በጀርመን ወረርሽኙን ለማዝገም የተወስዱትን እርምጃዎችን የማላልት ሂደት (exit strategy) በየ14 ቀኑ በሚከለሱ የተለያዩ ዕቅዶች እና ደርጃዎች ተጀምረዋል።

1. ሰራተኞችን በፈረቃ ማሰራት

የቀስ በቀስ ኮሮናን የማዝገም እርምጃዎችን የማላላት ሂደት ከሚመለከተው አንዱ ሰራተኞችን በፈርቃ ማሰራትን ነው። ቢሮ የግድ መግባት ያለባቸውም ከሆነ አቀማምጣቸው ፊት ለፊት እንዳይሆን፣ ሰፊ ርቀት በመካከላቸው እንዲኖር እና የአፈና አፍንጫ መከላከያ አድርገው እንዲቀምጡ ይሆናል። የመስሪያ ቤት ክለቦች፣ ሪስቶራንቶች እንደታገዱ ይቆያሉ። ወደ የመስሪያ ቤታቸው የሚገቡ ሰራተኞች መግቢያው ላይ ስማቸውን ያስመዘግባሉ።

2. የአፍና አፍንጫ ማስክ የማድረግ ግዴታ

በሙሉ ጀርመን በትራንስፖርት እና በመገበያየት ላይ የአፈና አፍንጫ መከላከያ ማድረግ ግዴታ ነው። ከዚህ ሳምንት ጀመሮ እጥረት የነበሩት ማስኮች በየቦታው፣ በየመድሃኒት መሸጫ ቤቶች መሸጭ ተጀምሯል።

3. ትምህርትን በፈረቃና ደረጃ በደረጃ ማስቀጠል

ትምህርት ቤቶች (ከአንደኛ ደርጃ እና ከመዋዕል ህፃናት በስተቀር) 4 May ሲጀመሩ፣ የአፍና አፍንጫ ማስክ ማድረግ ግዴታ ነው። ተራርቆ መቀመጥ እና በአንድ ክፍል ውስጥ ጥቂት ተማሪዎችን በማስተማር ይጀመራል። በብዙ ፌደራል ስቴቶች የሚወድቁ ተማሪዎች እንዳይኖሩ እና ወደ ሚቀጥለው ክፍል እንዲያልፉ፣ የሚደግሙት ክፍሉን ሳይሆን የወደቁበትን የትምህርት ዓይነት ብቻ እንዲሆን ተወስኗል።

4. በቤተክርስቲያን የጸሎት ስነስርዓት ላይ የታዳሚ መጠንን ውሱን ማድረግ
የቤተክርስትያን የፀሎት ስረዓት ከ15 ሰዎች በላይ የማይበልጥ፣ እያንዳንዱ ምዕመናን ስማቸውን የሚያስመዘግቡበት፣ ከቅዳሴ ውጭ የተለያዩ ዝግጅቶች፣ የመዝሙር ኮሮች የማይኖሩበት እቅድ ለውሳኔ ቀርቧል።

5. የቀብር ሥነ-ሥነስርዓት አካሄድ
ጀርመን አገር መካነ መቃብሮች በተወስነ ቀን ነው የቀብር ስነስረዓት የሚያስፈፅሙት። በሳጥን ያለ ሙሉ አስከሬኑ የሚቀበርበት ወይም ተቃጥሎ አመዱ የሚቀበርበት ቀናቶችም የተለያዩ ናቸው። በኮሮና አምካይነት የሀዘንተኛው ቁጥር ከ5 እንዳይበልጥ ሲደነገግ፣ ቀሪ ዘመዶች እና ቤተሰቦች ስነስረዐቱን በስካይፕ/ኦንላይን መከታተል ይችላሉ። የተገኙት ሰዎች ስምም ይመዘገባል።

6. የስፖርት ኩነቶች

የንክኪ ስፖርቶች በተለይም እንደ ማርሻል አርት ስፖርቶች እስክ 31 August ድረስ አንደተከለከሉ ይቆያሉ። ቢሆንም ፌዴሪሽኖች የኦንላይን የስፖርት አሰልጣኝነት እና የደረጃ ማሻሻያ ኮርሶችን ለማቅረብ እየሰሩ ነው። የጀርመን እጅ ኳስ ሊግ ሰንጠርዡን የሚመራውን ክለብ የአመቱ ሻምፕዮን በማድረግ አስቀድሞ አጠናቋል። ሆኖም ግን ሰው አልባ በሆነ ስቴድየም ውድድር ለማድረግ ከታሰበ ተጫዋቾች በየ3 ቀኑ ቴስት እንዲያደርጉ ታስቧል። ስለ ቡንድስሊግ እስካሁን የተወሰነ የለም። ጣልያን ከወሰድን ከ14 Mai ጀምሮ በተናጠል ልምምድ እንዲያደርጉ ታስቧል።

7. የውበት ሳሎን ስራዎች

ፀጉር ቤቶች ከ May 4 ጀምሮ ይከፈታሉ። ብዙ ጀርመኖች ፀጉራቸው በመርዘሙ በተለይም ለሴቶች የፀጉር ውበት መንከባክብ ባለመቻሉ የተቸገሩ ሲሆን የ Do-It-Yourself ፕሮግራሞች ብዙ ተከታይ አግኝተው ነበር። ፀጉር ቤቶች ሲከፈቱም ከፊት ጋር ንኪኪነት ያላቸው ግልጋሎቶች፣ ለወንዶች የፂም ቆረጣና ማሳመር፣ ለሴቶች የቅንድብና የፊት ማስዋብ ግልጋሎቶች አይኖሩም። የአፈና አፍንጫ መከላከያ ለደንበኛ እና ለሰራተኞች ማድርግ ግዴታ ነው።

8. የትያትርና ፊልም ቤቶች
ቲያትረኞች፣ ተዋንያን፣ የፊልም ቴክኒክ ሰራተኞች ወዘተ ከሚያገኙት 60 % ለመደገፍ ሲታቀድ ቲያትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶችን ለመደገፍ የመግቢያ ቲኬቶችን አስቀድሞ በመግዛት መድጎም ይቻላል (ለምሳሌ ለመስከረም ወይም ለጥቅምት)። የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወለድ የለሽ ብድር እንዲገኝ ተፈቅዷል። ይህም የውጭ አገር ተማሪዎችንም ያጠቃልላል።

9. የህዝብ በአላት አከባበርና ሰላማዊ ሰልፍ

May Day (1 May) ሚያዚያ 23 የዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን በጀርመን ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠው አመት በዓል ሲሆን የሰራተኛ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት በሚያዘጋጁት ዝግጅቶች እና በሰላማዊ ሰልፎችም የሚከበር ነው። በሌላው ጎኑ ደግሞ በጀርመን ፅንፈኛ የቀኝ በተለይም የግራ አክራሪዎች አዋኪ ሰላማዊ ሰልፎችን የሚያደርጉበት፣ ከዚያም አልፎ የሃብታምነት መግለጫ የሆኑ ውድ ሱቆችን፣ ንብረቶችን፣ መኪናዎች ላይ አደጋ የሚደርሱበት ነው። ይህንን በተመለከተ የወጣውን ደንብ በትንሽ ቡድን እና በተናጠል በመጣስ ለመንቀሳቀስ በተዘጋጁት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ የጀርመን ፖሊሶች እየተዘጋጁ ይገኛል። በበርሊን ከተማ ብቻ 5000 ፖሊሶች ይሰማራሉ።

10. የወንጀል፣ ማጨበርበርና ሀሰት ዜና

በጀርመን የቤት እና የተለያዩ የዝርፊያ ወንጀሎች በከፍትኛ ሁኔታ ሲቀንሱ። የሳይበር ወንጀል በተለይም የተጭበርበሩ ማስኮችን ማቅረብ፣ አጥማጅ ገፆችን (Phishing-Mail) በማቀርብ ማታለል፣ የሃሰት ዜናዎችን ማሰራጨት ጨምሯል።

11. መኪና ማሽከርከር

አፈና አፍንጫ መከላከያ አድርጎ የግል መኪና መንዳት በጭምብል አድርጎ የመንዳት ህግን ስለሚነካ ክልክል ነው። ያስቀጣል።

12. የኮረና በሽታ መከላከያ ካርድ/ሰርተፊኬት

የጀርመን ፌደራል መንግስት ከኮቪድ 19 ለዳኑ ለወደፊቱ ልዩ መብቶች ሊያመጣ የሚችል የኮሮና የበሽታ መከላከያ ካርድ (Immunity Certificates) ልክ እንደ ክትባት ሰርተፌኬት ለማውጣት አቅዷል።

 ኢትዮጵያ እስከዛሬ የሚደርጉ እርምጃዎች የሚያስመሰግን እና የሚያበረታታ ነው። አዲስ አበባ ጃንሜድ ላይ የመገበያያ ቦታ መሆኑ መልካም ነው። ጀርመን ሰዎች ርቀታቸውን ጠብቀው የሚቆሙበት ምልክቶችን መሬት ላይ ማድርግ እና ከዚያ ውጭ እንዳይነቃነቁ ማድረግ ግድ መሆኑን ያስተምረናል። ይህም ለጃንሜዳ እና ለመሳሰሉት የገበያ ማዕከላት መጠቀሙ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም በየክፍለ ከተማዎቹ ላይ ተመሳሳይ ጊዜያዊ የገበያ ማዕክሎችን ማስቀምጥ መጨናነቅን መቀንስ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ ብቃት እና እንቅስቃሴ የሚያሳድግ ነው።

 „ያንተ መብት የሚያቆመው የኔ መብት ጋር ሲደርስ ነው“ እንደሚባለው ቻንስለር ሜርከል የመብት እገዳዎች እና የዲሞክራሲ ትርጉምን በማስመልከት „ምክንያትዊ ዲሞክራሲ“ ያሉት የመብት ገደባን ሲገልፁ የምንቀበልው ዲሞክራሴ የራስን መብት ለማስጠብቅ የህብረተሰቡን የጤንነት መብት በመጠበቅ እንደሚገለፅ አስረድተዋል። ጀርመኖች ለዚህ ያበቃቸው ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የጤና ስርዓት፣ ዲስፕሊን፣ ቅንንነት፣ ፈጣን ውሳኔ፣ በመራራቅ የመቀራረብ አንድነት፣ ብልህ እና የስከነ ሁሉም የተሳተፉበት አካሄድ እና ፖለቲካዊ አመራር ነው። ይህም ጥሩ ውጤት ቢኖረም መዘናጋት እንዳይመጣ ከዚህ በፊት ርቀትን እና ንፅህናን ለመጠበቅ የወጣው መመርያ ተግባራዊቱ እንደቀጠለ ነው። በጀርመን በተመጠነ መልኩ እንቅስቃሴዎችን የመጨመርና ቁጥጥሮችን የማላላት እርምጃዎች ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ባለፉት አራት ተከታታይ ቀናት አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ በመምጣቱ የማላላቱ እርምጃ ተገቢ አልነበረም የሚሉ የባለሙያ ወቀሳዎችም እየቀረቡ ነው። ይህም ለኢትዮጵያ ምሳሌ የሚሆን ነው።

ከመልካም የጤናነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

Recommended For You

About the Author: admin